ኢህኣዴግ ወዴት፡ ክስመት ውይስ ውህደት?

Published by Ayele Gelan on

የዛሬ ሶስት አመት ገደማ፣ አንድ አንጋፋ የህወኣት ባለስልጣን፣ “ኢህኣዴግ ስልጣን የሚለቀው ከሃምሳ አመት በኋላ ነው” ብሎ ነበር። ለምን እስከ ሃምሳ አመት ስልጣን ላይ መቆየታቻው የግድ እንደሆነ ስተነትን እንዲህ ነበር ያለው፡ “የኢትዮጵያ ኤኮኖሚ አድጎ የቡርዡዋ መደብ ይፈጠራል። ከዚያ የብሄር ፖሎቲካ ያበቃለታል።  ያኔ ብሄር ላይ የተመሰረተ የፓርቲ ጥምረት አስፈላጊ አይሆንም። ኢህኣዴግ ይከስምና በመደብ ክፍፍል ላይ የተመሰረተ ፖሎቲካ ቦታውን ይይዛል!” በጣም ደስ የምትል፣ አካሄዷ ግልጽ የሆነች ልብ ወለድ ታሪክ ነበረች። ከሃምሳ አመት በኋላ፣ የነማን ልጆችና ልጅ ልጆች ካፒታሊስቶች ሆነው ሃብታቸዉን ለመጠበቅ ፓርቲ እንደሚመሰርቱ፣  የእነማን ልጆችና ልጅ ልጆች የሰራተኛ መደብ ሆነው ለደመወዝ ጭማሪ ሰልፍ እንደሚወጡ ሁሉ በምናባችን ቁልጭ ብሎ እስክታይ ድረስ የተተነበየች ቆንጆ ልብ ወለድ!

ያቺ ድርሰት ተጽፋ፣ ሃምሳ ይቅርና ግማሽ አመስት አመት እንኳን ሳይሆን፣ በነጎድጓድ የታጀበ ዶፍ ጣለባቸው፣ ያ ህልም በቅጽበት ወደ ቅዠት ተለወጠ። ኢህኣዴግ  ከእንቅልፏ ባንና ከተረጋግች በኋላ፣ አሁን ደግሞ ሌላ ትረካ ይዛ ብቅ አለች፡  “አምስት አስርት አመታት ቆይተን ለክስመት መዘጋጀት አስፈላጊ አይደለም፣ እንዲሁ በደፈናው እንወሃድ” የምትል።  ለምን መወሃድ አስፈለገ?  ለመወሃድስ የሚያስችል በቂ መሰረት አለ ወይ? እና ለመሳሰሉት ጥያቄዎች አጥጋቢ መልስ ያለ አይመስልም።  እንዲሁ በደፈናው ውህደት ተባለ። 

እንደ እውነቱ ከሆነ፣ የክስመት ልበወለድ ታሪክ የበለጠ ትጥማለች። ቢያንስ ቢያንስ ኪነታዊ ለዛ አላት፣ ታስቃለች። የኋለኛዋ ትርክት ግን በደንብ ለመተረክ እንኳን አትመችም። የጀማሪ ደራሲ ስራ ትመስላለች። 

ይሄ የኢህኣዴግ ዉህደት ነገር የሶሻሊሽምን ጽንሰ ሃሳብ መበከልን ተከትሎ የሰው ልጅ የከፈለውን መስዋእትነት አስታወሰኝ።  ካርል ማርክስ፣ ከካፒታሊዝም ወደ ሶሻሊዝም ለመሸጋገር፣ “የምርት ሃይሎች ጎልብተው እስኪያድጉ መጠበቅ የግድ ነው” ብሎ ነበር።  ሌኒን “መጠበቅ አያስፈልግም፣ አቋራጭ መንገድ አለ፣ የሽግግር ጊዜ መድቦ የምርት ሃይሎች እድገት ማፋጠን ይቻላል” አለ።  እናም ሌኒን ያለውን ተከተልን። በከፊል ገና ከጋርዮሽ ህብረተሰብ ብቅ እያልን ያለን ሁሉ የሌኒንን መንገድ ሞከርን። ዋጋ ከፈልን! የተከፈለው ዋጋ ምናልባትም ለህብረተሰብ እድገት ቁልፍ የመሆን ተስፋ አዝሎ የነበረው ሶሻሊሽም ከስሮ፣ ተወረወረ፣ ምናልባትም እስከናካቴው!

ላለፉት 28 አመታት ኢህኣዴግ ገዢ ፓርቲ ሆኖ ቆይቷል። በዚህን ጊዜ ሁሉ፣ ቢያንስ በጽንሰ ሃሳብ ደረጃ ተቀባይነት ልኖረው የምችልና፣ የኢትዮጵያን መሰተታዊ ችግር ለመፍታት ሲባል የተለያዩ የሀገሪቷን ህዝቦች የሚወክሉ ፓርቲዎችን አቅፎ ነበር።  ይህንን ህብረት እውነትም ያሉትን የሀገሪቷን መሰረታዊ ችግሮች ለመፍታት ሳይሆን፣ ለመሰሪና እኩይ ተግባር ሲጠቀሙበት ቆዩ።  የኢህኣዴግ ከፋፍለህ ግዛ ዘይቤ፣ የነበሩት ልይነቶችና ቅራኔዎች፣ ከሚገባ በላይ እንዲገዝፉ፣ ህዝቦች እንዲጋጩና በያካባቢው ግጭቶችና ፍጥጫዎች እንድሰፍኑ አደረገ። ኢህኣዴግ የዘራቸው ቅራኔዎች፣ የቀመራቸው ሸሮች አድገው ከቁጥጥር ውጪ ሆነው፣ አሁን ሀገሪቷ ለመበታተን ጫፍ ላይ ደርሳ ትታያለች።

በዚህ መካከል እንግዲህ ኢህኣዴግ “ውህደት” የምትለዋን ትረካ ይዛ ብቅ ያለችው። ውህደት ውስጥ የተደበቁ ምስጥሮች እንዳሉ ግልጽ ነው። 

1ኛ. የውስጥ ክፍፍልን መደበቅና ማድበስበስ ነው። ህወኣት ጭራሽ በውህደቱ አልታቀፈችም። አዴፓና ኦዴፓ ፍጥጫ ላይ እንዳሉ እናውቃለን።  ይህ በንዲህ እንዳለ ነው እንግዲህ  የ“ውህደት” ትረካ እየጦዘ ያለው። “ጎረቤት ሆነን መኖር አልቻልንምና እስቲ ደግሞ ቤተሰብ ሆነን እንሞከር፣ በዚያውም ጸባችን እንዳይታወቅብን ለመደበቅ ይመቻል” አይነት ሽንገላ።  አይመስልም፣ አያሳምንም! “Dhoksuun fanxoo hin fayyissuu” የምል የኦሮሞ ተረት አለ፣ “በመደባበቅ ከቂጢኝ አይዳንም” እንደ ማለት!

2ኛ. ኢህኣዴግ የርእዮተ አለም ኪሳራ እንደደረሰበት አመነ ማለት ነው። ብሄረሰቦች በጋራ ለመሰረቱት ፌዴራሊዝም ዘብ ቆመናል ስሉን ከረሙ።  ፌዴራሊዝሙን ግን ሲያለመልሙት ሳይሆን ሲያቀጭጩት ቆዩ። አሁን በአስራ አንደኛው ሰአት ወደ ህብረ ብሄር ሸርተት ማለት፣ የመሰረቱትን ብሄር ላይ የተመሰረተ ፌዴራሊዝምን ጥሎ መኮብለል መስሎ ይታየኛል። 

3ኛ. ከሁሉ በላይ ይሄኛው ሊሰመርበት ይገባል፤  ኢህኣዴግ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ያላወራረዳቸው ብዙ ሂሳቦች አሉዋት። ለውህደት ጥድፊያው እነዚያን በርካታ ወንጀሎች ለማድበስበስ ጭምር ይመስለኛል።  ከተጠያቂነት ለመሸሽ! 

ስለ ኢህኣዴግ ውህደት ሲነሳ ቢያንስ ቢያንስ እነዚህ ጉዳዮች ከግንዛቤ ውስጥ መግባት አለባቸው። ህዝብን የሚወክል ፓርቲ ቢኖር፣ እነዚህንና ከዚህ ጠጠር ጠንከር ያሉ ሃሳቦችን አንስቶ ያፋጥጣቸው ነበር።  ያንን ቁመና ያለው ቡድን ህገሪቷ እንዳሌላት ይሰማኛል።  ስለዚህ መልክቴ ለህዝቡ ነው።


Leave a comment:

Your email address will not be published. Required fields are marked *


CAPTCHA Image