ቢያንስ የማርች 8 እለት ወጣት ሴት ድምጿን የማሳማት መብት ሊኖራት ይገባል!

Published by Ayele Gelan on

የዛሬ 6 አመት ገደማ፣ አልጃዚራ ስትሪም (Aljazeera Stream) በተባለ ቲቪ ፕሮግራም ላይ፣ ጃዋር መሃመድ ተጋብዞ ውይይት ላይ እያለ፣ አወያይ ጋዜጠኛዋ እንዲህ ብላ ጠየቀችው፡ “ከኢትዮጵያነትህና ከኦሮሞነትህ የቱ ይበልጥልሃል?” ጃዋርም ሳያመነታ እንዲህ ብሎ መለሰ፡ “ኦሮሞነቴ ይበልጥልኛል! (I am Oromo First!)” ቀጠለናም “ኢትዮጵያዊነቴን በሚመለከት ገና ብዙ መስተካከልና መታረም ያለባቸው ጉዳዮች አሉ”

የኢትዮጵያን ጉዳይ በቅርብ ለምንከታተል ሁሉ፣ ይሄ የጃዋር መልስ ምንም የሚያስገርም ነገር አልነበረበትም። ጃዋር ይህን ከማለቱ በፊት ለአስርተ አመታት የአማራና የኦሮሞ ደያስፖራ ተለያይቶ ሳይቀላቀል ለየብቻቸው ሲኖሩ ሰንብተው ነበር። አብያተ ክርስቲያናት፣ ዓመታዊ የስፖርት በዓላትን፣ ወዘተ ለየብቻ አላቸው፣ እስከዛሬም ድረስ!

ይህን ስር የሰደደ መለያየትን ዝም ብሎ ሲመለከት የከረመ አዳሜ፣ ልክ ጀዋር ኦሮሞነቴ ይበልጥልኛል ያለ እለት መንገድ ላይ ወጥቶ መጮህ ጀመረ። በርካታ ሰላማዊ ሰልፎች በየክፍለ ግዛቱና ክፍለ ዓለማቱ ተካሄዱ። የጀዋርን ስም ለማጠልሸት ዶኩመንተሪዎችን እስከመፈብረክ ተኬደ።

ምስጋና ለነዚያ ጩሀተኞች፣ እነዚያ አልጃዚራ ስቱዲዮ የተሰነዘሩ ሁለት ተራ ቃላትን፣ ተከትሎ ዘላቂ ህዝባዊ እንቅስቃሴ መሰርት ተጣለ። የ “Oromo First Movement” ተወለደ። በኦሮሞ ደያስፖራ መካከል የነበረው ክፍተት ተዘጋ። የኦሮሞ ወጣቶች ከዳር እስከዳር ተንቀሳቀሱ። ጉልበታቸውንና እዉቀታችውን አቀናጁ። OMN ወዲያው ተወለደና ድምጽ ለተነፈገውና ለዘመናት ድምጹ ታፍኖ ለኖረ የኦሮሞ ህዝብ ድምጽ ሆነ። የቄሮ አብዮት አቀጣጣለ። ቀሪው ታሪክ ነው ነው ምባለው፣ the rest is history!

አሁን ተመሳሳይ ነገር ሊከሰት እንደሆነ ይታየኛል። ትናንትና አንዲት የኦሮሞ ወጣት የተሰማትን ተናገረች። ይታያችሁ ይህቺ ወጣት አስተያየቷን የሰጠቺው ማርች 8ን ለማክበር በተዘጋጀ በዓል ላይ ነው። እንደተለመደው እዬዬው ቀጠለ። በማርች 8 እንኳን የኦሮሞ ወጣት ሴት ድምጽ ለምዝጋት ዘመቻ ተከፈተ። ቀውጢ ወረደ።

ለአቅመ ትንተና ያልበቁ እንጭጭ ጋዜጠኞች በቲቪ መስኮት ብቅ አሉ፣ ተንጫጩ። ለምን ቢባል መልሱ አጭር ነው፣ኦሮሞን አፍ መመዝጋት! የመንግስት ባለስልጣናት ያለ ምንም ሀፍረት መግለጫ ሰጡ። ዛቻ አከሉበት። ደብል ስታንዳርድ ይሉዋል ይሄ ነው።

ማንም ውርጋጥ ዘግናኝና አጸያፊ አባባሎችን ስጠቀም ምንም አይባልም። “አማራ የሰው ሁሉ የውሃ ልክ ነው፣ ከሁሉ ሰው በላይ ነን” እያለ የፖለቲካ ድርጅት ሃላፊነት ላይ ያሉ ሁሉ በሚዲያ እንተርቪው ሲሰጡ ማንም ትንፍሽ አላለም። “ይህን ሀገር የፈጠርነው እኛ ነንና እግዜር ስለፈጠረን እንደምናመልከው ሁሉ፣ እኛንም አምልኩን” ቢባልም ይህ አባባል አጸያፊ ነው ያለ አልነበረም።

ለኦሮሞ ድምጽ ግን መንግስት እየተከተለ ያለው ዜሮ ቶለረንስ ፖሊሲ ይመስላል። በኦሮሞ የፖለቲካ ቡድኖችና ሚዲያዎች ላይ የሚደረገው ከልክ ያለፈ ጫና አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል። ማንም ወገንተኛነቱ ግልጽ የሆነ ግለሰብ የመንግስት አካል ስለሆነ ብቻ ሰበብ ፈልጎ የኦሮሞ ተቋማትንና ግለሰቦችን እንደፈለገ ማስፈራራት የተለመደ ሆኖዋል።

መታወቅ ያለበት ነገር ይህ ነው፣ ይሄ ኦሮሞን ሰበብ ፈልጎ የማስቦካት ዛቻ (bullying tactic) ውጤቱ ሀገሪቷ ውስጥ ሰፍኖ ያለውን የውጥረት ድባብ ማክረር ብቻ ነው።

ይህን አጭር መልእክት ስጽፍ፣ OMN ይቅርታ መጠየቁን ሰማሁና እጅግ በጣም አዘንኩ። እስከምገባኝ ድረስ OMNን ይቅርታ የሚያስጠይቅ አንድም ጥፋት የለም፣ OMN ለምን እንዳጎበደደ ግን ይገባኛል፣ ጥፋት እንዳሌለባቸው ጠንቅቀው ያውቃሉ፣ ውጥረቱን ለማብረድና ወርቃማ ጊዜን ላለማባከን እንደሆነ ይገባኛል።

አሊያማ እንኳንስ OMN፣ ያን አስተያየት የሰጠች ልጅ እንኳን ይቀርታ መጠየቅ የለባትም ባይ ነኝ። ጥፋት የለማ!


Leave a comment:

Your email address will not be published. Required fields are marked *


CAPTCHA Image